የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ መልአከ አርያም ቀሲስ ብርሃኑ ጎበና መልዕክት
“ሰላምንም አደርጋለሁ፤ክፋትንም አመጣለሁ።” ትንቢተ ኢሳይያስ 45፤ 7
የሰዎች ልጆች ክፉ ሥራ በምድር ላይ እየበዛ፣ የልባቸው ዐሳብ ምኞትም ሁል ጊዜ ፍጹም ክፉ እየሆነ በሚመጣበት ጊዜ እግዚአብሔር ያዝናል፤ በዚህም የተነሳ መቅሰፍት በምድር ላይ በሚኖሩ ክፉ አድራጊዎች ላይ ይታዘዛል።እግዚአብሔር ክፉ ነገርን በሰው ልጅ ላይ የሚያመጣው ህልውናውን ለማሳወቅና ክፉዎች ከክፋታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ነው “በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት፤ተመለሱ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ፤ረዳታቸውም እግዚአብሔር፥መድኃኒታቸውም ልዑል አምላክ እንደሆነ አሰቡ።” ተብሎ እንደተጻፈ መዝ.77፤34።
የእግዚአብሔር መቅሰፍት በምድር ላይ በታዘዘ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ኖኅና ሎጥ ሞገስ ያገኙ መቅሰፍቱ እንዳያገኛቸው አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተነገራቸውን ሊያደርጉ የሚገባቸውን በማድረግ የመአቱን ጊዜ በረድኤቱ ጥላ ሥር ተጠልለው ያሳልፋሉ።
በመቅሰፍት ጊዜ የእግዚአብሔር ሰዎች ከመቅሰፍቱ ይድኑ ዘንድ ምን ማድረግ ይገባቸዋል?
በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያገኘው ኖህ መአቱ ከመምጣቱ በፊት ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ነበር “ጌታ እግዚአብሔር ለባሪያዎቹ ለነቢያት ያልገለጠውንና ያልነገረውን ምንም አያደርግምና” በማለት ነቢየ እግዚአብሔር አሞጽ እንዳሰገነዘበው ትን.አሞጽ 3፤7።መአቱ እንደሚመጣ እግዚአብሔር አምላክ አስቀድሞ ነግሮት ነበርና፤እርሱና ቤተሰቦቹ ከመቅሰፍቱ የሚድኑበትን መርከብ ሰርቷል፤ ዓለማችን ታላቅ ህውከት ውስጥ እንደምትገባ መጻያትን የማወቅ ሀበት የተሰጣቸው አባቶች ቀደም ሲናገሩ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው፤ከሚመጣው መአት ለመዳን በኖህ መርከብ የተመሰለ ቤተ መቅደስ ሰውነታችንን በንስሐ ከኃጢአት፣ ከበደል አንጽተን በሥጋ ወደሙ ታትመን እንድንገኝ ቀድመው አሳስበውናል።
ደዌው በመላው ዓለም ተንሰራፍቶ ዓለም በምጥ ጣር ውስጥ ትገኛለች፤መላው የሰው ዘር በጭንቅ ማዕበል ተውጦ ባለበት በዚህ ወቅት እንደሎጥ ከመቅሰፍቱ ስፍራ ራስን ማራቅ ግድ ነው።“የሚሰማኝ ግን በተስፋ ይኖራል፥ከክፉም ሁሉ ያለ ድንጋጤ ያርፋል” እንደተባለ ምሳሌ 1፤33።በእግዚአብሔር ልንመካና እሱን ተስፋ ልናደርግ ”አሁንስ ተስፋዬ ማን ነው ?እግዚአብሔር አይደለምን“ በማለት ተስፋውን በእግዚአብሔር ላይ ያደረገው ቅ.ዳዊትን አብነት ልናደርግ ይገባል፤እንዲሁም እንደ ክርስቲያን ልባሞችና ጥንቁቆች እንሆን ዘንድ ቅዱስ መጽሐፍ የሚነግረንን ልንፈጽም ይገባል “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ማስተዋልም ይጋርድሃል” እንዳለ ጠቢቡ ሰሎሞን ምሳሌ 2፤11።አምላካችን ከክፉው ደዌ እንዲሰውረን እየጸለይን ራሳችንን ከቫይረሱ እንድንጠብቅ በባለሙያዎች የሚነገረውን ተግባራዊ ማድረግ በእግዚአብሔር አለመታመን እንደሆነ አድርጎ ከሚያስብ አእምሮ ነጻ መሆን ይገባል፤በእግዚአብሔር ጥበቃ ውስጥ የሰው ድርሻም መኖር እንዳለበት መዘንጋት የለበትም።ሕይወታችን በተአምር ብቻ የሚመራ አድርጎ የሚያሳስብ መንፈስ ካለ ልንቃወመው ይገባል ትክክለኛው ፍኖተ እግዚአብሔር አይደለምና።ክርስቲያን የሚገባውን የእርሱን ድርሻ እየፈጸመ ከእርሱ አቅም በላይ ያለውን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ይሰጣል እንጂ ሁሉን እግዚአብሔር ይሰራዋል በሚል ግብዝነት አይገበዝም።የሚገባውን ካደረገ በኋላ “በልዑል መጠጊያ የሚኖር፣ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል።እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፣አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥በእርሱም እታመናለሁ።እርሱ ከአዳኝ ወጥመድ፥ከሚያስደነግጥም ነገር ያድንሃል።” መዝ.90(91)፤1-3።የሚለውን አምላካዊ ቃል በማሰብ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ማድረግ ይገባል ከዚህ አልፎ አምላክ እንደሌላቸው አህዛብ በጭንቀት ማዕበል ተውጦ የሚይዙትንና የሚያደርጉትን ማጣት ከክርስቲያኖች አይጠበቅም።
እግዚአብሔር መአቱን አርቆ፤ ምህረቱን ያውርድልን::
“ሕዝቤ ሆይ፥ ና ወደ ቤትህም ግባ፥ ደጅህን በኋላህ ዝጋ ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ።” ትንቢተ ኢሳይያስ 26 ፤ 20
ውድ የክርስቶስ ቤተሰቦች ምዕመናን “በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ” ብሎ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቅዱስ ጢሞቲዎስ እንደተናገረው እነሆ ዛሬ በዘመናችን መላው ዓለም በጭንቀት ማዕበል ተውጦ ይገኛል፡፡ ዳሩ ግን ክርስትያኖች እንደመሆናችን “እግዚአብሔር ከክፉ ሁሉ ይጠብቅሃል ፥ ነፍስህንም ይጠብቃታል፡፡” ተብሎ በቅዱስ ዳዊት እንደተነገረው መዝሙር 120፥6፡፡ ተስፋችን የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ዓለምን እያስጨነቀ ካለው ክፉ ደዌ እንደሚጠብቀንም ልናምን ይገባል፡፡ ተስፋ እንደሌላቸው እንደ አህዛብ ልንሸበር አይገባም ፤ ዳሩ ግን ከጸሎት ጋር ልናደርገው የሚገባውን ማንኛውንም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ “ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይጋርድሃል” መጽሐፈ ምሳሌ 2፥11 ፡፡ ተብሎ እንደተገለጸው ልናደርገው የሚገባውን ማንኛውንም ጥንቃቄ በግብዝነት ወይንም በስንፍና ሳናደርግ ቀርተን መከራ ቢመጣብንና እግዚአብሔርን ብናማርር የሚፈይደው ፋይዳ የለም፡፡
የኮሮና ቫይረስ የስርጭት አድማሱን እያሰፋ በመምጣቱ የቫይረሱን መዛመት ለመግታት በመንግስት በኩል እየተወሰዱት ካሉት እርምጃዎች አንዱ በስብሰባዎች ላይ የተሰብሳቢዎችን ቁጥር መገደብ ነው፡፡ በዚህ መሰረት የሜሪላንድ አገረ ገዢ እጅግ አነስተኛ ቁጥር ያለው ስብስብ ብቻ እንዲደረግ ያሳሰቡ ሲሆን ይህን ተላልፎ መገኘት እርምጃ የሚያስወስድ መሆኑን ተገልጿል ፡፡ ስለሆነም እገዳው በአዋጅ እስከሚነሳ ድረስ ምእመናን በቤታችሁ ሆናችሁ እንድትጸልዩና በካህናቱ መሪነት የሚደርሰውን የረቡዕና የአርብ የሰርክ ምህላና ጸሎት (6:30 am to 8:00 am) ፥ የእሁድ ቅዳሴ በኦንላየን (Online) እንድትከታትሉ እናስገነዝባለን፡፡
“ቍጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ” እንደተባለ ሁላችሁም በቤት ሆናችሁ መልካሙን ዘመን አምላካችን እንዲያመጣልን እንድትጸልዩ እናሳስባለን ፡፡
እግዚአብሔር በጎውን ዘመን ያምጣልን፡፡
መልአክ አርያም ብርሃኑ ጎበና
የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ