ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ

‹‹ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ::›› (የሐዋ 3÷2)

March 05, 2021    በኩረ  ትጉኋን ቀሲስ አብርሀም አንዳርጌ

“ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ” የዚህ ኃይለ ቃል ተናጋሪው ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ ነው። ቅዱስ ጴጥሮስ እና ቅዱስ ዮሐንስ ለጸሎት ወደ ቤተ መቅደስ በተገኙበት ሰዓት በቤተ መቅደሱ ደጃፍ የተቀመጠ ከእናቱ ማህጸን ጀምሮ አንካሳ የነበረ አንድ ሰው እንዲመጸውቱት እንደለመናቸውና እነርሱም ለእርሱ የሚሰጡት ብርና ወርቅ እንደሌላቸው ነገር ግን ፈቃደኛ ከሆነ ካለበት ደዌ ሊፈውስት እንደሚችሉ ነግረውታል። ይህ ሰው ለዘመናት እንደልቡ እንዳይንቀሳቀስ ሽባ አድርጎት ከነበረው ደዌ ተፈወሰ። ተፈውሶም በደስታ እየዘለለ እግዚአብሔርን ሲያመሰግን በእርሱ መፈወስ እጅግ ተደንቀውና ተገርመው ለሚመለከቱት አይሁድ ያስተላለፈው መልእክት ነው። እናተም የክርስቶስን ወደዚህ ዓለም ሰው ለማዳን መምጣት ባለማወቃችሁ ለመስቀል ሞት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት ስለዚህ ያ የሰራችሁት ” ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ ተመለሱ።” (የሐዋ 3÷2) በማለት አስተማራቸው። የዚህ ትምህርት ዋና ዓላማ ክርስቲያኖችን ከኃጢአት እንዲርቁ ማድረግ እና በኃጢአት ቢወድቁ እንኳን በንስሐ ኃጢአታቸው እንደሚሰረይላቸው ማስገንዘብ ነው።

1. ኃጢአት ምንድነው?

ኃጢአት ማለት በአጭሩ በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ ነው። የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ መጣስ ማለት ነው። ይህም ማለት “አድርግ” የተባለውን አለማድረግ ወይም “አታድርግ” የተባለውን ትዕዛዝ መጣስ ማለት ነው። የሰው ልጆችን ኃጢአት በሁለት ዓይነት መንገድ ለይተን ማየት እንችላለን የመጀመሪያው የአዳም ኃጢአት (ጥንተ አብሶ) ሲሆን ሁለተኛው ራሳችን ነጻ ፈቃዳችን ተጠቅመን የምንፈጽመው ኃጢአት ነው።

ከጥንተ አብሶ በፊት አዳም በጥንተ ተፈጥሮው የቅድስናና የጽድቅ ጸጋ ነበረው።እግዚአብሔር በመዘንጋቱና ሕጉን በመተላለፉ የተሰጠውን ጸጋ ተገፈፈ እርቃኑንም ቀረ። በፈጸመው በደል ማፈርና መደንገጥ ከፈጣሪውም መደበቅ ጀመረ (ዘፍ.3÷1-8) ይህ ነበር የበደሉ ውጤት የውድቀቱ ታሪክ የተጀመረበት። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በመጀመሪያው በደል ምክንያት የአዳም የነፍስና የሥጋ ባሕርይ በኃጢአት ስለ ተመረዘና በፈጣሪው ስለተረገመ የሰው ተፈጥሮ ኃጢአትና ሞት የሚስማማው ሆነ። እንግዲህ ይህ የቅድስናና የጽድቅ ጸጋ የተለየው የኃጢአት ይዞታና ሁኔታ በእርግማን ሥር ካለው ከአዳም ወደ ልጆቹ ተላለፈ። የእግዚአብሔር ቃል እንደሚናገረው በአዳም አለመታዘዝ ሰው ሁሉ ከአዳም ዘር የመጣ በመሆኑ ኃጢአተኛ ሆኖ ተቆጠረ። “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤”(ሮሜ 5:12) ኃጢአት ወደ ዓለም የገባው በአዳም ነው። እኛ ሁላችን የሰው ልጆች የአዳም ልጆች ስለሆንን ኃጢአተኛ ሆነን ተገኘን።

ጌታችን አምላካችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ አዳም ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ በዕለተ ዓርብ በደሙ ካሣ ሲከፍል ያንጊዜ የአዳምና የዓለም ኃጢአት ሁሉ ተደምስሷዋል።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጥንተ አብሶ በሰው ልጆች ላይ አይገኝም የተባለው በክርስቶስ አምነው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ለተጠመቁት ክርስቲያኖች ብቻ ነው። ነገር ግን ላላመኑትና ላልተቀበሉት የዕለተ ዓርቡ የምሕረት አዋጅ ለእነርሱ ተፈጻሚነት የለውም።ስለዚህ ነው ያመነ የተጠመቀ ይድናል ይህንን ያላመነ ግን ይፈረድበታል ተብሎ በወንጌል የታወጀው (ማር.16÷16) ጌታችንም በዚህ ምክንያት ነው ሐዋሪያትን ስለ ሥርየተ ኃጢአት እንዲሰብኩና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ያዘዛቸው። (ሉቃ.24÷47)

ሁለተኛው የኃጢአት አይነት ደግሞ ነፃ ፈቃዳችንን ተጠቅመን የምንፈጽመው ክፋ ነገር ሁሉ የግል ኃጢአታችን ነው።ይህንንም በሦስት መንገድ እንፈጽማለን።በሐሳብ (በሀልዮ) ፣ በመናገር (በነቢብ) እንዲሁም በመተግበር (በገቢር) እንፈጽማለን። አንደኛው በሐሳብ የማይገባውን በማሰብና በመመኘት በልቡና ኃጢአት ይፈጸማል።በሌላ በኩል ደግሞ የሚገባውን መልካሙን ነገር አለማሰብም ኃጢአት ይሆናል። ሁለተኛው በመናገርም ኃጢአት ይሰራል። ስድብን በመናገር ወይም የማይገባውን ሰውን የሚጎዳውን ነገር በመሠወር ፈንታ ገልጾ በማሳወቅ ፣ በመናገር ፣ በመጻፍ እና በሐሜት በመናገር (የቃል) ኃጢአት ይፈጸማል። በአንጻሩ ደግሞ የሚገባውን ያለመናገር ፣ መመስከር የሚገባውን በእውነት ሳይመሰክሩ መቅረትና በዚህም የተነሳ በሰው ላይ ጉዳት የሚደርስ ከሆነ ታላቅ በደል እንደተፈጸመ ይቆጠራል። ሦስተኛው በስራም እንደዚሁ ክፉ ማድረግ ፣ የማይገባውን መፈጸም ኃጢአት ይሆናል። በአንጻሩ የሚገባውንና የታዘዘውን መልካም ስራ አለመፈጸምም እንደዚሁ ኃጢአት ነው።

ሰው ለኃጢአት ካለው ዝንባሌ የተነሳ ከነዚህ ከሦስቱ በአንዱ ኃጢአት መውደቁ የማይቀር ነው።ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ “ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።”(1 ዮሐ 1÷8) ስለዚህ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለምንሰራው ኃጢአት ሁሉ መድኀኒቱ ንስሐ ነው። ኃጢአታችንን ሰምተው የሚረዱን “ኃጢአቱን ይቅር ያላችሁት ይቅር ይባልለታል” ተብሎ ኃጢአትን የማስተስረይ ሥልጣን የተሰጣቸው ካህናት ናቸው። (ዮሐ 20÷23)

2.  ንስሐ ምንድነው?

ንስሐ ማለት ነስሐ ተጸጸተ ፣ ተመለሰ ካለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ይህም የሰራነውን ኃጢአት የሚያስተስርይ ምስጢር ነው። ለዚህም ነው ቅዱስ ጴጥሮስ “ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ።” (የሐዋ 3÷2) ንስሐ ጸጸትን የሚያመለክት ቢሆንም ቁጭትና አለማዊ ጸጸት ሳይሆን እውነተኛ ኀዘን ሆኖ ወደ ኑዛዜ የሚወስድ መሆን አለበት። ስለዚህ ማንኛውም ሰው ንስሐ መግባት ከክፉ ስራው መመለስ ፣ መጸጸት አለበት። በዚህም ምስጢረ ንስሐ ሰው ከእግዚአብሔር የኃጢአትን ስርየት ያገኛል ፤ ጸጋውን በረከቱንም ይታደላል። ንስሐ እግዚአብሔር ደካማውን የሚያበረታበት የወደቀውን የሚያነሳበት መንገድ መሆኑን ነብየ እግዚአብሔር ኤርምያስ ይናገራል ” እግዚአብሔር እንዲህ ይላል የወደቁ አይነሡምን? የሳተስ አይመለስምን?” (ኤር.8÷4) በማለት ንስሐ ኃጢአተኛ ወደ እግዚአብሔር የሚመለስበት ደገኛ ሥርዓት መሆኑን ያስተምረናል።

ምስጢረ ንስሐን የመሠረተልን ለስም አጠራሩ ክብርና ምስጋና ይግባውና ጌታችን አምላካችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሰው በኃጢአት ተይዞ ሳለ በመስቀል ተሰቅሎ በሕማሙና በሞቱ አንድ ጊዜ አድኖናል።ከዚያ በኃላ ለምንፈጽመው ኃጢአት ማስተሰረያ እንዲሆን ለሐዋርያቱና ተከታይ ለሆኑት ካህናት ሥልጣን በመስጠት ምስጢረ ንስሐን መስርቶልናል። “መንግሥተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ፤ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማያት የታሰረ ይሆናል፥ በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል።” (ማቴ 16÷19 ማቴ.18÷18)

ንስሐ ገብተን የኃጢአት ስርየት አግኝተን ከሰውና ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀን በጽድቅ ጎዳና ለመራመድ ቢያንስ ሶስት ነገሮችን መፈጸም ይኖርብናል። የመጀመሪያው የንስሐ ኀዘን ነው። ንስሐ የሚገባ ሰው መጀመሪያ የሰራውን ኃጢያቱን እያስታወሰ ሰውንና እግዚአብሔርን በደልኩ ብሎ ከልብ የሚያዝነው ኃዘን ነው። ይህ ወደ ንስሐ የሚደረግ እውነተኛ ጉዞ ነው። ” የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው ፤ መጽናናትን ያገኛሉና።”(ማቴ.5:4) ። ሁለተኛው ኑዛዜ ነው። በሰራው ኃጢአት ከልቡ ያዘነ ሰው ቀጣዩ ሂደት የሰራውን ኃጢአት ሳይቀንስ ሳይጨምር ለካህን መናዘዝ ነው።ስንናዘዝ ከካህኑ ጋር የሚሰማን እግዚአብሔር መሆኑን አምነን መሆን ይኖርበታል። ” ኃጢአቱን የሚሰውር አይለማም፤ የሚናዘዝባትና የሚተዋት ግን ምሕረትን ያገኛል። (ምሳሌ 28÷13) ሦስተኛው ቀኖና እና ፍትሐት ነው። ተነሳሒው ለካህኑ ኃጢአቱን ከተናዘዘ በኃላ ሁለት ነገሮችን ይቀበላል።ቀኖና እና ፍትሐት። ቀኖና ማለት ለኃጢአቱ ምክርና ተግሳጽ የሚያገኝበት ሲሆን ፍትሐት ማለት ከኃጢአት እስራት የሚፈታበት ነው። ቀኖናውን ሲጨርስ ጸሎተ ንስሐ ይጸለይለታል። ካህኑ እግዚአብሔር ይፍታህ ይለዋል። በኑዛዜ ወቅት ካህኑ ለተነሳሂው ያዝናል ፣ ይጸልያል ፣ ምክሩን ይለግሰዋል ፣ ተስፋ ይሰጠዋል ፣ ያጽናናዋል። ቀኖና ኃጢአት ሞትን እንደሚያስከትል እንደሚያስቀጣ እንዲያውቅ የሚሰጥ ነው። እንደ ኃጢአቱ ሁኔታ ቀኖና ይሰጠዋል።

ኃጢአትን ለካህን መናዘዝ ለምን አስፈለገ የሚለውን እንመለከትና ትምህርታችንን እናጠቃልላለን። የሰው ልጅ ነጻ ፈቃዱን ተጠቅሞ ለሰራው ኃጢአት ቅጣቱን ይቀበላል። የሰራውን ኃጢአት በንስሐ አባቱ ፊት ቀርቦ መናዘዙ በራሱ ቅጣት ነው። በዚህም ያ ሰው ዳግመኛ የካህኑን ፊት ለማየት በማፈር እንደዚያ ያለ ኃጢአትን በድጋሚ እንዳይፈጽም ይረዳዋል። ኃጢአትን አምኖ ለካህን መናዘዝ ለእግዚአብሔር መናዘዝ ነው። ” ኢያሱም አካንን ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጥ ለእርሱም ተናዘዝ ያደረከውንም ንገረኝ አትሸሽገኝ አለው።” (ኢያ 7÷19) በዚህም መሠረት ካህናት ዐእይንተ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ዓይኖች) ተብለው ይጠራሉ። በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን በለምጽ ደዌ የተመታውን ሰው ወደ ካህን ሂድ ሲለው እንመለከታለን “…ኢየሱስም፡— ለማንም እንዳትናገር ተጠንቀቅ፥ ነገር ግን ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ሙሴ ያዘዘውን መባ አቅርብ፡ አለው።” (ማቴዎስ 8÷4) በመሆኑም ኃጢአትን ለካህናት መናዘዝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።ሌሎች እንደሚሉት ከተጸጸትን በቂ ነው እርሱ የልብን ያውቃል መናዘዝ ለእግዚአብሔር ብቻ ነው…ወዘተ በሚል ራስን ኃጢአት በሚያለማምድና ከንስሐ የሚያርቅ ኢ-መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምሮችን ልንቃወም ያስፈልጋል።

በመጨረሻም ንስሐ መግባት ታላቅ ጸጋ መሆኑን ማወቅ ይገባል። ንስሐ ዘማዊውን እንደ ድንግል ፣ ኃጥኡን ጻድቅ ፣ ቀማኛውን መጽዋች የምታደርግ ደገኛ ሥርዓት ናት። ንስሐ የሰው ልጆች ስለ ኃጢያታቸው ተጸጽተው ከእግዚአብሔር ጋር እንዳይታረቁ በብርቱ በሚጥረው ሰይጣን ላይ የሚገኝ ታላቅ ድል ነው።ይህንን ሁሉ ጠቃሚ ነገሮችን ተገንዝበን ጊዜ ሳንሰጥ ዛሬውኑ ልባችንን ወደ ንስሐ ሕይወት መመለስ ይኖርብናል። ጌታችን በወንጌል “ነገ ለራሱ ይጨነቃልና ለነገ አትጨነቁ…” (ማቴ.6÷34) ብሏል። የዚህ ትርጉሙ ዛሬ ንስሐ ገብቼ ነገ ኃጢአትን ብሰራስ ብላችሁ አትጨነቁ ዛሬ የሰራችሁትን በዛሬው ዕለት ንስሐ ግቡ ነገ ደግሞ ለምትሰሩት በነገው ዕለት ንስሐ ትገባላችሁ ማለቱ ነው። እነሆ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “የመዳን ቀን ዛሬ ነው” እንዳለው በመነሻችንም ቅዱስ ጴጥሮስ “ኃጢአታችሁ ይደመሰስ ዘንድ ንስሐ ግቡ።” (የሐዋ 3÷2) እንዳለው። ወደ አባቶቻችን ቀርበን ተናዘን በንስሐ ሳሙና ታጥበን ፤ የንስሐ ፍሬን አፍርተን አዲስ ሰው እንድንሆንና በመጨረሻም ቅዱስ ስጋውን በልተን ክቡር ደሙን ጠጥተን የመንግስቱ ወራሾች እንድንሆን አምላካችን በቸርነቱ ይርዳን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር