‹‹እንደተማራችሁት በሃይማኖት ጽኑ›› (ቆላ. ፪፥፯)
July 15, 2020 ዲያቆን ዮሴፍ በቀል(ምንጭ : ከማኅበረ ቅዱሳን ድህረ ገጽ )
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ሃይማኖታቸውን እንዲያጸኑ ታስተምራለችና በሃይማኖታችን ልንኖር ይገባል፤ ሃይማኖት የእግዚአብሔርን ህልውና ማወቅ ለእርሱ መታመን ነውና ምእመናን ሁሉ በሃይማኖት መጽናት አለብን፡፡ ይህም በሕይወታችን የሚመጣብንን መከራ እና ፈተና ሁሉ በትዕግሥት እንድናልፍ ይረዳናል። ቅዱስ ጳውሎስ አስቀድሞ ለቆላስይስ ምእመናንን ማስተማሩን በማስታወስ እኛ ክርስቲያኖች በቅድሚያ የተማርነውን ትምህርት አጽንተን በሃይማኖት እንድንቆይ ነግሮናልና።
ዓለም በአዘጋጀችው ማታለያ ቁስ (መደለያ) ሰዎችን ለማሳት ቀን ከሌሊት እየዳከረች ትገኛለች። ስለዚህ የመጀመሪያዋን እውነተኛዋን እምነት አጽንቶ ያልያዘ ሰው ፈጽሞ የክርስቶስን መንግሥት ተካፋይ እንዳልሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስረዳ ‹‹የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናል›› ብሏል፡፡ በዚህም የመጀመሪያዋን እምነት አጽንተው ያልያዙትን ሁሉ ጌታችን በመጨረሻ ‹‹አላውቃችሁም›› እንደሚላቸው የታወቀ ነው። እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናግሯልና፤ ‹‹በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።›› (ዕብ. ፫፥፲፬፣ ማቴ. ፯፥፳፩-፳፫)
ቅዱስ ጳውሎስም ‹‹ቀኖቹ ክፍዎች ናቸውና›› ዘመኑን ዋጁ ብሎ እንዳስተማረን በእምነት ጉዳይ ላይ ቅንጣት ታህል ድርድር አያስፈልግም፤ ያለንበት ዘመን ክሕደት፣ ምንፍቅና የበዛበት እጅግ ክፉ ነው። ጥንቱንም የሰው ልጆችን ከእግዚአብሔር መለየት ሥራው የሆነው ጠላት ዲያብሎስ ዛሬም ሆነ ወደፊት ሠራዊቶቱን (አጋንንትን) በማሰማራት ምንፍቅናን እና ክሕደትን እያስፋፋ ሰዎች ጣዖትን እንዲያመልኩ እያደረገ ይገኛል። (ኤፌ. ፭፥፲፮)
ቅዱስ ጴጥሮስ ይህን አስመልክቶ ‹‹ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡዋቸዋል›› በማለት የዘመናችን የጥፋት ባሪያዎች መሆናቸውን እንዳስተማረን እነዚህ ለመንጋው የማይራሩ ጨካኝ ተኩላዎች እንደሚነሱ ቀድሞ ነግሮናል፡፡ እንዲሁም ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሀለሁ፤ እምነትና በጎ ኅሊና ይኑርህ፡፡ አንዳንዶች ኅሊናቸውን ክደው ልክ መርከብ አለመሪ እንደሚጠፋ ሁሉ በእምነት ጉድለት ጠፍተዋልና›› ብሎ ለመንፈስ ቅዱስ ልጁ ለጢሞቴዎስ እንደነገረው እኛም ከጠፉት ጋር እንዳንጠፋና ከክርስቶስ መንግሥት የተለየን እንዳንሆን የተሰጠንን በሃይማኖት በመጽናት መወጣት ይኖርብናል።›› (፪ኛ ጴጥ. ፪፥፲፱፤ ፩ኛ ጢሞ. ፩፥፲፱)
በዚህ የምትኖር ነፍስ በሚገጥማት ፈተናዎችና መከራዎች ለበለጠ ትዕግሥት ትነሣሣለች እንጂ አትደክምም፡፡ ‹‹መከራ ብርቱውን ሰው ይበልጥ ብርቱ ያደርገዋል›› እንዲል፤ ይኸውም ልክ ኢዮብን ይበልጥ ጽኑዕ እንዳደረገው ነው፤ ዝናቡ ወረደ ማለትም እሳት ከሰማይ ወደቀች፤ በጎቹን ሁሉ አቃጠለች። ጎርፍም መጣ ማለትን አንዱ መልእክተኛ ተናግሮ ሳይጨርስ ሌሎች መልእክተኞችም አሁንም አሁንም እየመጡ የከብቶቹን፣ የግመሎቹን፣ የልጆቹን መጥፋት ነገሩት፤ እንዲሁም ‹‹እግዚአብሔርን ስደብና ሙት›› የሚለው የሚስቱ መራራ ቃል አስጨነቀው፤ ያ የኢዮብ እምነት አልላላምና ያ ጻድቅ ሰው አላጉረመረመምና፤ አልፎ ተርፎ ‹‹እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ፤ እግዚአብሔር እንደ ፈቀደ ሆነ›› ብሎ አመስግኗል። (ኢዮ. ፪፥፱፤ ኢዮ. ፩፥፳፩)
ለመከራዎቻችን ሁሉ አምላካችን እግዚአብሔር መፍትሔ የሚሰጥበት ጊዜ አለ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው መጸለይ፣ በሃይማኖትም መኖር ነው፡፡ ይህም በጎ ምግባር እንድንፈጽም ይረዳናል። ራስችን ለማጥፋት ከምንፈልገው በላይ እግዚአብሔር እሳቱን ያጠፋልን ዘንድ ይፈልጋል፤ ነገር ግን ንስሓችንን (መመለሳችን) እየጠበቀ ነው። መከራ ከዕረፍት እንደሚመጣ ሁሉ ከመከራም በኋላ ዕረፍትን መጠበቅ ግድ ነው፤ ስለዚህ መከራ ቋሚ አይደለም፤ ሰላም አለ ግን ከእኛ ዘወትር እግዚአብሔርን መለመን እና ማመስገን ይጠበቃል።
ሠለስቱ ደቂቅ ወደ እሳት ቢጣሉም ግን ሃይማኖታቸውን አልረሱም፤ ነበልባሉም አላስፈራራቸውም፤ በእልፍኝ ከተቀመጡ ሰዎች በላይ ሆነው በምንም ነገር ሳይፈሩ በነበልባሉ እሳት ተከበው ሳሉ ወደ ፈጣሪያቸው ይጸልዩ ነበር። ስለዚህ እሳቱ ለእነርሱ እንደ ግምብ እና አጥር ነበር፤ ነበልባሉም እንደመጎናጸፊያ ነበር። በተቃራኒው በነበልባሉ አቅራቢያ የነበሩት በእሳቱ ተቃጠሉ። ሆኖም የእነርሱ ሃይማኖት ከበረ፤ በዚህም ንጉሥ ናቡከደኖፆር መኳንንቱ፣ ሹማምቱ፣ አማካሪዎቹ እና የሀገሪቱ ሕዝቦች ሁሉ የእግዚአብሔርን ድንቅ ተአምር አይተው እንዲመለሱ ሆነ። ጠላት የፈለገውን ሴራዎቹን ቢያበዛባቸውም ልጆቹን ይበልጥ አበረታቸው፡፡ በዚህም በጆሮአቸው የሚሰሙት የጠላት ድምጽ፣ በዓይናቸው የሚያዩት አስፈሪው የነበልባል እቶን እሳት እንዳልነበረ ሆነ፤ በሃይማኖት እሳቱን እና ንጉሡን ገዙት። (ዳን. ፫፥፪)
ስለዚህ እኛም ኃጢአት ሠርተን እግዚአብሔርን ካላሳዘነው በቀር ሺህ ጊዜ ወደ እቶን እሳት ብንጣል እንኳን ምንም አይነካንም፡፡ ተስፋ አንቁረጥ! እግዚአብሔርን አሳዝነን እንደ ሆነ ግን እንቀጣለን፡፡ እነዚህ ታዳጊዎች ምንም ሳይበድሉ በእቶን ውስጥ ነበሩና እቶኑ በፍጹም አልጎዳቸውም፡፡ ነገር ግን አንድ ሰው ራሱን እስከ ጎዳ ድረስ የቦታው መልካም መሆን እርሱን መልካም አያደርገውም፡፡ ልክ እንደዚህም የቦታው መጥፎነትም በሁሉም ረገድ ራሱን ለሚያበረታ ሰው አይጎዳውም፤ ስለዚህ እኛም በሁሉም ረገድ ራሳችን እናበርታ። በነፍስ መሞት እንጂ በሥጋ መሞት ሃይማኖታችንን አያሳጣንምና፤
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን በማስመልከት ‹‹እንደ እባብ ልባሞች ሁኑ›› ብሎናል፡፡ እባብ ራሱን ለማዳን ሲል ዋናው አካሉን (ጭንቅላቱን) ለአደጋ እንደማያጋልጥ ሁሉ እኛም እንዲሁ እናድርግ፡፡ ሃይማኖታችን ለመጠበቅ ስንል ምድራዊ ሕይወታችን ወይም ሀብት ንብረታችንን ሁሉ እንኳን መስጠት ካለብን እንስጥ፡፡ ይህንንም በማድረጋችን በፍጹም አንዘን! እኛ ሃማኖታችንን ይዘን ወደ ወዲያኛው ዓለም ስንሄድ እግዚአብሔር ደግሞ ሁሉንም ነገር እጅግ ውብ አድርጎ ይሰጠናል፤ ከምድራዊ ሀብትና ንብረት ይልቅ በረከትን ይሰጠናል፡፡ ቅዱስ ኢዮብ ዕራቁቱን ሆኖ በዐመድ ላይ ከሞት የበለጠ አስከፊ ሕይወትን እንደመራ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል፡፡ ነገር ግን ሃይማኖቱን ስላልተወ አምላክ አስቀድሞ ከሰጠው ሀብትና ጸጋ ሁሉ እጅግ አብዝቶ መልሶለታል፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚበልጥ አክሊለ ትዕግሥትን አግኝቷል። (ማቴ. ፲፥፲፮)
ሃይማኖት ካለን ሀብት ባይኖረን ወይንም ኑሮአችን ቢከፋም በትዕግሥት መከራውንና ችግሩን አልፈን ሁሉንም ከቀድሞ ይልቅ ታላቅ በሆነ ክብር እናገኘዋለን። ስለዚህ ከልክ በላይ የሆነ ድሎትን ከእኛ በማስወገድ ወደ ራሳችን ልንመለስ ይገባል፡፡ በዚህም አሁን ካለው ቸነፈር እንጠበቃለን፡፡ እግዚአብሔርም ከቁጣው ወደ ምሕረት ይመለስልናል፡፡ በፈተናን ጸንተን በተስፋ እንድንኖር ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ይርዳን፤ አሜን።