ሃይማኖት ለምን ያስፈልጋል?

‹‹በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን›› (ምሳ. ፫፥፯)

 

September 21, 2020 (ምንጭ : ከማኅበረ ቅዱሳን ድህረ ገጽ )

ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌው ‹‹በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን›› ሲል በዘመናት በሚነሡ  የተለያዩ ፍልስፍናዎች በመተማመንና በመመካት ሰዎች ከእግዚአብሔር አምላክ ርቀንና ጠፍተን እንዳንቀር አሳስቧል፡፡ ዓለማዊ ዕውቀት ብቻ ወይንም ፍልስፍና ወደ ተሳሳተ መንገድ በመውሰድ ሰዎች ፈጣሪያቸውን እንዲክዱ እና ፈጣሪ የለም እስከማለትም እንዲደርሱ ያደርጋልና፡፡ (ምሳ. ፫፥፯)

በተለይም በቅርብ ጊዜ ከተነሡት ፍልስፍናዎች አንዱና እጅግም የተስፋፋው የኢ-አማንያን አመለካከት ማለትም ‹‹ሃይማኖት የጦርነት ምንጭ ነው፤ ስለዚህ አያስፈልግም›› በሚል ክርስትናን እና ተዋሕዶ ሃይማኖትን በመንቀፍ ለቤተ ክርስቲያን መቃጠልና ለበርካታ ምእመናን ሞት መንሥኤም ሆኗል፡፡ ይህ የምዕራባውያን አስተሳሰብ የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና መጋፋትና የተዋሕዶ ሃይማኖት አረንቋ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ስለሆነም ከምን ጊዜውም የበለጠ ክርስቲያኖች በሃይማኖት እና በእምነት ሊጸኑ እንደሚገባ እንረዳለን፡፡

ከማንኛውንም የፍልስፍና ዓይነት ወይንም አስተሳሰብ የሚልቀው የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ስለመሆኑ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ፡፡ ሀልዎተ እግዚአብሔርን ተረድተንን እና ዐውቀን በእምነት ሁሉን እንድንመረምር የአምላካችን ፈቃዱ ነው፡፡ እምነት ከዕውቀትና ከፍልስፍና ይበልጣልና፡፡  (ቀሲስ መልካሙ ካሣ ስብከት እና ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ መጽሐፍ ‹‹ትምህርተ ሃይማኖት መቅድም››)

‹‹በሕገ ልቡና በምርምር መንገድ ከአሕዛብ ወገን ብዙዎች ወደ እግዚአብሔር ዕውቀት የደረሱ እንዳሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ምስክሮች ናቸው፡፡ ከቤተ እስራኤልና ከቤተ ክርስቲያን እምነት ውጭ በጥንተ ጊዜ በምዕራብ እንደ ግሪኮችና ላቲኖች፣ በምሥራቅ እንደ ፋርስ ባቢሎን እንደ ሕንድ፣ ቻይናና የመሳሰሉት ሁሉ የፍልስፍና ሃይማኖትና የአምልኮ ሥርዓት እንደነበራቸውና እንዳላቸው የታወቀ ነው፡፡ እንዲያውም በፍልስፍናው ዓለም ከነበሩት ዋና ዋናዎቹ በተለይም የግሪክ ፈላስፎች በአንድ አምላክ በማመናቸው የተነሣ ፍልስፍና ከክርስትና ሃይማኖት ጋር በአንድ ሁኔታ ተገንዝቦ ይገኝ ነበር፡፡

በዘመነ ሐዋርያት የነበረው የፍልስፍና ዓይነት ለክርስትና መስፋፋት እንደረዳ በብዙዎች ዘንድ ይታመናል፡፡ የእስክንድርያ የትርጓሜ ትምህርት ቤት መምህርና መሪ የነበረው ቀሌምንጦስ ይህን ሐሳብ ይደግፍ ነበር፡፡ በእርሱ አመለካከት ‹‹ብሉይ ኪዳን አይሁድን በሞግዚትነት አሳድጎ ለክርስቶስ ለወንጌል እንዳስረክብ፤ አሕዛብንም መርቶ ወደ ክርስቶስ ያደረሳቸው ፍልስፍናቸው እንደሆነ ገልጦ ይናገር ነበር፡፡››

አንዳንድ ሰዎች በፍልስፍና በእግረ ልቡና ተጉዘው የእግዚአብሔርን ሀልዎት ወደ ማመን ለመድረስ ቢችሉም በአንጻሩ ሌሎች ደግሞ በልዩ ልዩ ምክንያት ወደ መጠራጠር፣ ክሕደት እና ወደ ባዕድ አምልኮም የሄዱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ያም ሆነ ይህ እውነተኛው አምልኮት እግዚአብሔር በእርግጠኝነት ሊታወቅ የሚችለው በራሱ በእግዚአብሔር አጋዥነት ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን ከመውደዱ የተነሣ ሐሰትን ከእውነት፥ ክፉውን ከበጎ ለይተው እንዲያውቁ መጠራጠርን እና ክሕደትን አስወግደው እንዲሁም በእርሱ ብቻ አምነው ልጆቹ እንዲሆኑ አስቦ ከጥንት ጀምሮ በመረጣቸው ወገኖች አማካይነት ለዓለም ሁሉ ያዘጋጀውን የማዳን ምሥጢር ቀስ በቀስ በጊዜው ገለጠላቸው፡፡ በመጀመሪያ በቤተ እስራኤል ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መገለጥ ለዓለም ሁሉ ተነገረ፡፡ በፊተኛው በትንቢት፥ በታሪክና በምሳሌ በኋላው በአማናዊነትና በፍጹምነት ተገልጧል፡፡ እንግዲህ በሕገ ልቡና ወደ ተገለጠው አምላክ እንዲመጡ ጥንትም ሆነ ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታሰማለች፡፡ ወደ አማናዊው ሃይማኖት ኑ፥ ከዚህ የኅሊና ሰላምና ዕረፍት ይኖራችኋል፤ በእምነትና ጸጋውም እፎይታ ታገኛላችሁ፤ ወደ ፊትም የበለጠው ተስፋና ደስታ ይጠብቃችኋል ትላለች፡፡ የሰው ልጅ ደኅንነትና ሕይወት በክርስትና እንጂ በፍልስፍና እንዳልሆነ እያስረዳች ከአምላክ የተገለጠውን የወንጌል ምሥራች ቃልን እንዲያምኑ ለሁሉም ወገኖች ታስተምራለች፡፡

በሕገ ልቡናም ሆነ በተራቀቀ ፍልስፍና የተገኘው የሃይማኖት ዕውቀት ሰው በተፈጥሮ ዕውቀቱና በውሱን አእምሮ ተመራምሮ የደረሰበትን ነገር እውነት ነው ብሎ በሕሊናው የተቀበለው ወይም ሊሆን ይችላል ብሎ በስሜቱ የሚደግፈው የእምነት ዓይነትና የአምልኮ ሥርዓት እንጂ እውነተኝነቱን ከራሱ ውጭ በሆነ ኃይል አላረጋገጠም፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር መገለጥ የተገኘው እውነተኛ ሃይማኖት ከሰው አእምሮ በላይ በሆነ ኃይልና ጥበብ የተከናወነ ስለሆነ ከሁሉም የሃይማኖት ዓይነት እጅግ የላቀ ነው፡፡ ከሌላው ሊወዳደርም አይገባውም፤ በዓይነቱና በሁኔታው፣ በይዘቱና በመልእክቱ፣ በትምህርቱና በተአምራቱ ከማንኛውም አንጻር ብንመለከተው ከሌላው እጅግ የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለሆነም የሰው ልጅ ይህንን እውነት በልቡናው ሁኔታ በእምነት ሲቀበል በታላቅ አክብሮትና በደስታ ይኖራል፡፡ ይልቁንም የመገለጡ ሁኔታ ከሰው ልጆች የመዳን ምሥጢር ጋር የተያያዘ ስለሆነ እምነቱን የሚቀበለው ከምስጋና ጋር ነው፡፡

እንግዲህ በድንቁርና ጨለማ ምክንያት የመጣው መጠራጠርና ክሕደት በእግዚአብሔር መገለጥ መወገዱን፣ እውነተኛው የዕውቀት ብርሃን መታየቱን፣ የመዳኑም ተስፋ መምጣቱን የተገነዘበ ልቡና ሁሉ ይህን ላደረገለት ፈጣሪ የሚሰጠው ምላሽ ምንድን ነው? ‹‹ምንተኑ አዐስዮ ለእግዚአብሔር በእንተ ኵሉ ዘገብረ ሊተ፤ ስላደረገልኝ ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ምን እከፍለዋለሁ›› እንዲል፡፡ ትክክለኛው ምላሽ በእግዚአብሔር ማመንና መተማመን ለእርሱም የሚገባውን የምስጋና መሥዋዕት ማቅረብ ነው፡፡ እግዚአብሔር ለሰው በማዳን ጸጋውና ፍቅሩ ከመገለጥ የበለጠ ሌላ ነገር የለምና፡፡  (መዝ. ፻፲፭፥፫)

በምርምር የሚገኘው የፍልስፍና ሃይማኖት በተፈጥሮ የታወቀውንና በሥነ ፍጥረት የሚታየውን መሠረት አድርጎ የሚሄድ የዚህ ዓለም ምድራዊ ጥበብ ስለሆነ ከተወሰኑት ክልል ውጭ አልፎ ወደ እውነተኛው የእግዚአብሔር ጥበብ ሊደርስ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ጥበብ የተባለው እንደ ተፈጥሮ ዕውቀት ለሁሉም ክፍት ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የሚታወቅ በምሥጢራዊነት የሚገኝ ስለሆነ ነው፡፡ ‹‹ያልፍ ዘንድ ያላቸው የዚህ ዓለም ነገሥታት፥ ፈላስፎች የሚያውቁት ጥበብ አይደለም፡፡… ጥበብም ያልኹት ኅቡእ ክቡር የሚሆን ሥጋዌ ነው››  በማለት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እስኪገለጥ ድረስ ከዓለም ፈላስፎች ተሠውሮ ስለነበረው መለኮታዊ ጥበብ ያስረዳሉ፡፡ (፩ኛ ቆሮ.፪፥፮-፯ አንድምታ ትርጓሜ)

የእግዚአብሔር ጥበብ የተባለ ይህ ምሥጢረ ሥጋዌ ለሰዎች ልጆች ክብር የተዘጋጀው የደኅንነትና የሕይወት፥ የእውነትና የጽድቅ መንገድ እንደሆነ ከሐዋርያው ጳውሎስ እንማራለን፡፡ ዓይን ያላየችው ጆሮም ያልሰማው በሰው ልብ ያልታሰበው፣ ዓለም ሳይፈጠር እግዚአብሔር ለሚወዱት ያዘጋጀውን፣ ተሰውሮም የነበውን የእግዚአብሔርን ጥበብ በምሥጢር ሐዋርያው  አስተምሯል፡፡ ይህም ተሰውሮ የነበረው የመዳን ምሥጢር ከአዳም ተስፋ ጀምሮ ቀስ በቀስ በደረጃ በቅዱሳን አበውና ነቢያት አማካኝነት ተገልጦ በመጨረሻም በሥጋ በተገለጠውና በመጣው በክርስቶስ ተፈጽሟል፡፡ ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረ የእግዚአብሔር ቃል እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ፤ ሰውም ሆኖ፤ በሥጋ ተገለጠ›› በማለት ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የምትመሰክረው በተሰጣት መለኮታዊ መገለጥ መሠረት እንጂ በሰው ሠራሽ ፍልስፍና አይደለም፡፡ መለኮታዊ መገለጥ ሁሉ ስለ ሰዎች ደኅንነት ነው፡፡

በብሉይ ኪዳን የተነገረው የተስፋ ቃል ሁሉ ከእግዚአብሔር የተገኘ ነው፡፡ የትንቢቱም፥ የተስፋውም ቃል የሚያተኩረው በአካላዊ ቃል መገለጥ ስለተገኘው የመዳንና የዘለዓለም ሕይወት እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር መገለጥ ከሰው ልጆች የመዳን ታሪክ ጋር ተነጣጥሎ አይታይም፡፡ ምክንያቱም በልዩ ልዩ ጊዜያትና ሁኔታዎች የታየው መለኮታዊ መገለጥ ሁሉ የራሱ የሆነ ዓላማና መልእክት እንዳለው ከቅዱሳት መጻሕፍት መረዳት ይቻላል፡፡ ስለሰዎች መዳን ካልሆነ በስተቀር እግዚአብሔር ስለራሱና ለራሱ ብቻ ብሎ አይገለጥምና፡፡ የእግዚአብሔርን ህልውና በማወቅና እርሱን ድጋፍ በማድረግ ዕውቀትን እናገኝ ዘንድ በእምነት እና በሃይማኖት ልንኖር ይገባል፡፡››

እግዚአብሔር አምላክ ወደ ፍጹም ዕውቀት ያደርሰን ዘንድ ይርዳን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ ‹‹የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም›› በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ