የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ

‹‹የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ›› (ዮሐ.፪፥፲፮)

March 11, 2020 ( ምንጭ : ከማኅበረ ቅዱሳን ድህረ ገጽ )

በዐቢይ ጾም ሦስተኛው ሳምንት በእለተ እሑድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ወስጥ በቤተ መቅደስ በሬዎችንና በጎችን፥ ርግቦችንም የሚሸጡትን፥ ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፡፡ ይህን ባለመውደዱም የገመድ ጅራፍ ካበጀ በኋላ በጎችንና በሮዎችን እንዲሁም ሁሉንም ከቤተ መቅደስ አስወጣቸው፤ የሻጮቹንም ገንዘብ በተነባቸው፤ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፤ ርግብ ይሸጡ የነበሩትን ደግሞ ‹‹ይህን ከዚህ አውጡ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉ አላቸው፡፡›› (ዮሐ.፪፥፲፬-፲፮)

ከዚህ በኋላ ጌታችን በአይሁድ ምኩራብ ገባ፤ በዚያም የተሰበሰቡትንም ዝም ይሉ ዘንድ ከገሠፃቸው በኋላ አስተማራቸው፡፡ እንዲህም አላቸው፤ ‹‹ከመሥዋዕት ይልቅ ምሕረትን እወዳለሁ፤ የሰንበት ጌታዋ የምሕረት አባቷም እኔ ነኝ፤ የሰው ልጅም የሰንበት ጌታዋ ነው፡፡ ያባቴን ቤት የንግድ ቦታ አታድርጉት፤ ቤቴስ የጸሎት ቤት ይባላል፡፡››  እነርሱም ወደ ትምህርቱን፣ የቃሉን ግርማ፣ የአነጋገሩን ጣዕምና፣ የአንደበቱን ቅልጥፍና አደነቁ።

ምንባባት

በዚህ ወቅት ጌታችን ወንጌልን ባስተማረው መሠረት እና መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተመዘገበውም እንዲህ ይነበባል፡፡

እንግዲህ በመብልም ቢሆን÷ በመጠጥም ቢሆን÷ በልዩ ልዩ በዓላትም ቢሆን÷ በመባቻም ቢሆን÷ በሰንበትም ቢሆን የሚነቅፋችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፡፡ ይህ ሁሉ ይመጣ ዘንድ ላለው ጥላ ነውና። አካሉ ግን የክርስቶስ ነው፡፡ በመታለልና ራስን ዝቅ በማድረግ ለመላእክት አምልኮ ትታዘዙ ዘንድ ወድዶ÷ በአላየውም በከንቱ የሥጋው ምክር እየተመካ የሚያሰንፋችሁ አይኑር፡፡ ሥጋ ሁሉ ጸንቶ በሚኖርበት÷ በሥርና በጅማትም በሚስማማበት÷ በእግዚአብሔርም በሚያድግበትና በሚጸናበት በሚሞላበትም በራስ አይጸናም፡፡ (ቆላ. ፪÷፲፮)

ከዚህ ዓለም ኑሮ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ እንደገና በዓለም እንደሚኖሩ ሰዎች እንዴት ትሠራላችሁ? እንዴትስ ይህን አትዳስስ÷ ይህን አትንካ÷ ይህንም አትቅመስ ይሉአችኋል? ይህ ሁሉ እንደ ሰው ትእዛዝና ትምህርት ለጥፋት ነውና፡፡ ይህም ስለ ልብ ትሕትናና እግዚአብሔርንም ስለ መፍራት÷ ለሥጋም ስለ አለማዘን ጥበብን ይመስላል፤ ነገር ግን ከሥጋ በላይ ነው እንጂ ምንም ክብር የለውም፡፡

ወንድሞቻችን ሆይ÷ እምነት አለኝ፤ ምግባር ግን የለኝም የሚል ሰው ቢኖር÷ ምን ይጠቅመዋል? በውኑ እምነቱ ልታድነው ትችላለችን? ከወንድሞቻችን÷ ወይም ከእኅቶቻችን÷ የታረዙ ወይም የዕለት ምግብ ያጡ ቢኖሩ÷ ከእናንተም አንዱ÷ “በሰላም ሂዱ÷ እሳት ሙቁ÷ ትጠግባላችሁም” ቢላቸው÷ ለችግራቸውም የሚሹትን ባይሰጣቸው ምን ይጠቅማቸዋል? እንዲሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው፡፡  (ያዕ. ፪፥፲፬)

ነገር ግን አንድ ሰው÷ አንተ እምነት አለህ÷ እኔም መልካም ሥራ አለኝ፤ እስቲ ሃይማኖትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፤ እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል፡፡ አንተም እግዚአብሔር አንድ እንደ ሆነ ታምናለህ፤ መልካምም ታደርጋለህ፤ እንዲህስ አጋንንትም ያምናሉ፤ ይንቀጠቀጣሉም፡፡ አንተ ሰነፍ ሰው÷ እምነት ያለ ምግባር የሞተች እንደ ሆነች ልታውቅ ትወዳለህን? አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን ወደ መሠዊያው ባቀረበው ጊዜ÷ በሥራው የጸደቀ አይደለምን? እምነት ለሥራ ትረዳው እንደ ነበር÷ በሥራውም እምነቱ እንደ መላችና ፍጽምት እንደ ሆነችም ታያለህን? አብርሃም በእግዚአብሔር አመነ፤ ጽድቅ ሆኖም ተቈጠረለት” የሚለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ፡፡ ሰው በሥራ እንደሚጸድቅ በእምነት ብቻም እንዳይደለ ታያለህን? እንዲሁ ዘማይቱ ረአብ ደግሞ ጒበኞችን ተቀብላ÷ በሌላ መንገድ ባወጣቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ÷ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው፡፡

ግብረ ሐዋርያት

በቂሳርያም ቆርኔሌዎስ የሚባል አንድ ሰው ነበር፤ ኢጣሊቄ ለሚሉት ጭፍራም የመቶ አለቃ ነበር፡፡ እርሱም ጻድቅና ከነቤተሰቡ እግዚአብሔርን የሚፈራ ነበር፤ ለሕዝቡም ብዙ ምጽዋት ይሰጥ ነበር፤ ዘወትርም ወደ እግዚአብሔር ይጸልይ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክም በራእይ ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት በግልጥ ታየው፤ ወደ እርሱም ገብቶ÷ ቆርኔሌዎስ ሆይ÷ አለው፡፡ ወደ እርሱም ተመልክቶ ፈራና÷ አቤቱ÷ ምንድን ነው? አለ፤ መልአኩም እንዲህ አለው÷ “ጸሎትህም ምጽዋትህም መልካም መታሰቢያ ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ዐርጎአል፡፡ አሁንም ጴጥሮስ የሚባለውን ስምዖንን ይጠሩልህ ዘንድ ወደ ኢዮጴ ከተማ ሰዎችን ላክ፡፡ እርሱም ቤቱ በባሕር አጠገብ ባለው በቊርበት ፋቂው በስምዖን ቤት እንግድነት ተቀምጦአል፡፡ ልታደርገው የሚገባህን እርሱ ይነግርሃል፡፡ (የሐዋ.፲፥፩-፰)

እግዚአብሔር አምላክ ምሕረት ይሰጠን ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር