‹‹እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ›› (፩ኛቆሮ.፲፫፥፩)
March 11, 2019 ዲያቆን ዮሴፍ በቀለ ( ምንጭ : ከማኅበረ ቅዱሳን ድህረ ገጽ )
ጸናጽል ድምፁ መልካም የሆነ የምስጋና መሳርያ በመሆኑ ከቀደሙት ሌዋውያን አሁን እስካሉት የሐዲስ ኪዳን ቤተ መቅደስ መዘምራን ፣ ከቀደመው የሙሴ ድንኳን ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ይዘነው የምንቆመው መሳርያ ነው፡፡ ምስጋናችንም ሆነ መዝሙራችን ያለከበሮና ጸናጽል ምን ውበት ሊኖረው ይችላል ብለን እንጀምራለን? አንጀምረውም፡፡ የሊቃውንቱ መዳፍ ያለ ጸናጽል አይንቀሳቀስም፣ ቅኔ ማኅሌቱም ያለ ከበሮ አይደምቅም ፤ እንደ ጾመ ኢየሱስ ያለ ቀን ካልገጠመው በስተቀር ቅኔ ማኅሌት ከነዚህ ነገሮች አይለይም፤ ይገርማል! ዳሩ ግን አንድም ቀን ቢሆን በዚህ ሁሉ የአገልግሎት ዘመናቸው ወደ ቤተ መቅደስ ገብተው ለሥጋውና ለደሙ ክብር በሚደረገው አገልግሎት ተሳትፈው አይተናቸው አናውቅም፤ ጥንትም ሆነ ዛሬ አገልግሎታቸው ከውጭ ብቻ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ የባዶ ሕይወት ተምሳሌት አድርጎ ተጠቅሞበታል፤ “የሰውን ሁሉ ልሳን ባውቅ፣ በመላእክትም ቋንቋ ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ነሐስ፤ እንደሚንሿሿም ጸናጽል ነኝ” (፩ቆሮ ፲፫÷፩) ይላል፡፡ ይህን ስመለከት ከልጅነቴ ጀምሮ በቤተ መቅደሱ ያደገች ነፍሴን አሰብኩና እስራኤል ሲማረኩ “ጽዮንን ባሰብናት ጊዜ አለቀስን” ብለው እንደተናገሩ እኔም ለተማረከችውና ባዶዋን ለቀረችው ጽዮን ሰውነቴ አለቀስኩላት፤ ከኔ በቀር ጽዮን ሰውነቴ ባለተስፋ ምድር መሆኗን ማን ያውቅላታል? የተገባላትንስ ቃል ኪዳን ከኔ በቀር ማን ያውቅላታል?
ስለዚህ ደጋግሜ በባቢሎን ወንዞች አጠገብ ሆኜ ምርር ብየ አለቀስኩላት፤ ደግሜ ደጋግሜም እንዲህ አልኳት፤ እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደ ሚንሿሿም ጸናጽል ነሽ አልኳት፡፡ እስኪ አስቡት! ያለኔ ማኅሌቱ አይጀመር፣ ዝማሬው አይደምቅ ፣ የሊቃውንቱ ጉሮሮ አይከፈት፣ ሽብሻቧቸው አያምርበት ፣ እጃቸው ያለኔ አይንቀሳቀስ፣ ቅኔው አይጸፋ፡፡ እስኪ ንገሩኝ! ምኑ ነው ያለኔ የሚያምረው፤ በየትኛው አገልግሎት ነው እኔ የማልገባው፤ የትኛውስ ሊቅ ነው ያለኔ በእግዚአብሔር ምስጋና ላይ የተገኘው ፤ ጥንትም ሆነ ዛሬ እኔ ለዚች ቤተ መቅደስ አገልግሎት አስፈልጋለሁ ፡፡
ያለበለዚያማ ማኅሌቱ ምን ውበት ሊኖረው፤ ማንስ ነው እኔ በሌለሁበት ያለ እንቅልፍ የሚያገለግለው፤ ከከበሮው ተስማምቶ በሚወጣው መልካሙ ድምፄ ብዙዎቹ ይመሰጣሉ፣ የድምፄን ውበት በውስጠኛው ጆሯቸው እየሰሙ እንዲህ አሳምሮ የፈጠረኝን “ድምፁ መልካም በሆነ ጸናጽል አመስግኑ” እያሉ ያመሰግናሉ፡፡ የድምፄን መልካምነት ብቻ እየተመለከቱ ወይ መታደል ብለው ያደንቃሉ፤ እኔ እስከማዜም ድረስ በጉጉት ይጠባባቃሉ ፤ሰው ሲዳር፤ ሲሞትም ሆነ ሲሾም ያለኔ ምኑ ያምራል፤ አምጡት፣ አምጡት ይባላል፡፡
ይህን ሁሉ ክብሬን አየሁና በሰዎች መካከል በኩራት ተቀምጨ ሳለሁ ከዕለታት አንድ ቀን የሥጋየን መጋረጃ ግልጥ አደረግሁና ነፍሴን ተመለከትኋት፤ ትጮኻለች! አዳመጥኳት፤ ላደርገው የሚገባኝን እንኳን ያለደረግሁ፤ የማልጠቅም ባሪያ ነኝ፡፡ እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደሚንሿሿም ጸናጽል ሆኛለሁ እያለች ታንጎራጉራለች፡፡
የሚጎሰመው ነጋሪት፣ የሚመታው ከበሮ፣ የሚንሿሿው ጸናጽል ለራሳቸው ምን ተጠቅመዋል? ከነሱ በኋላ እየተነሣ ስንት ትውልድ ነው የእግዚአብሔርን መንግሥት የወረሰ፣ ከተስፋው የደረሰ፤ ሌላው በነሱ ተጠቅሞ አድማሳትን በቅድስናው ሲያካልል፣ መላእክትን ሲያክል፤ እነሱ ግን አሁንም ምድራውያን ናቸው፡፡ በዚህኛው ትውልድም አልተለወጡም፤ ጌታ እስኪመጣ ከዚህ ዓይነት ሕይወት የሚወጡም አይመስሉም፤
እኔም እንደነሱ ነኝ! ቃሉን እሰብካለሁ፣ ዝማሬውን እዘምራለሁ፣መወድሱን እቀኛለሁ፣ሰዓታቱን አቆማለሁ፤ ኪዳኑን አደርሳለሁ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከዳር አንብቤአለሁ፡፡ ዳሩ ግን መች እኖርበታለሁ ፤ ሰዎቹ ከአፌ የሚወጣውን ቃሉን እየሰሙ የሕይወቴ ነጸብራቅ እየመሰላቸው ይገረማሉ፤ እንደኔ ለመሆን ይቀናሉ፤ እኔ ግን ሳላስበው እንደሚጮኽ ነሐስ፣ እንደሚንሿሿም ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡ እጮኻለሁ እንጅ ለምን እንደምጮኽ እንኳን አላውቅም፤ በምጮኸው ጩኸት ከቶ አልለወጥም፤ ከኔ በኋላ እየተነሱ ብዙዎቹ ከምሥራቅና ከምዕራብ እየመጡ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ገብተዋል ፤ ከኔ በኋላ ቃሉን የሰሙት በቃሉ ተለውጠው ንስሓ ገብተዋል፡፡ እኔ ግን ዛሬም ሳያውቅ እንደሚጮሕ ነሐስ፣ ሳይወድ እንደሚንሿሿውም ጸናጽል ሆኛለሁ፡፡
የምጮኸው ገብቶኝ ቢሆንኮ ከኔ የሚቀድም ማንም አልነበረም፡፡ ነገር ግን ይህ እንዳይሆን ሕይወት የሌለኝ ቆርቆሮ ነኝ፤ ድምፄ መልካም ነው፣ ትጋቴ ግሩም ነው፡፡ ከምስጋናው ጋር መስማማቴ፣ በሁሉም እጅ መግባቴ መልካም ነበር፤ ሆኖም ፍቅር የለኝምና ምን ይሆናል፡፡ ሥጋየን ለሰማይ አዕዋፍ ብሰጥ ፣ያለኝንም ለድሆች ባካፍል ፣ የድሆች አባት ብባል ፣አጥንቴም እስኪታይ ብጾም ብጸልይ ፍቅር ግን ከሌለኝ ያው እንደሚጮኸው ነሐስ እንደሚንሿሿውም ጸናጽል መሆኔ አይደለ? ሥጋውን ደሙን ካልተቀበልኩ የኔ መጮኽ ምን ሊጠቅም ! ለካ ለሥጋውና ለደሙ የሚያስፈልገው በበጎ ዝምታ ዝም ያላለው እንደኔ የሚንሿሿው ጸናጽል አይደለም ብላ ነፍሴ ስታለቅስ እኔንም አስለቀሰችኝ ፡፡
ኦ!አምላኬ ጸናጽልነቴን ለውጥልኝ፣ነሐስነቴን አርቅልኝ!